በቡታጅራ ከተማ ታላቅ ህዝባዊ ተቃዉሞ ተደረገ | የሳዲቅ አህመድ የቪድዮ ዘገባ ከጽሁፍ ጋር

0
510

በደቡብ ክልል በጉራጌ ዞን በመሰቃን ወረዳ በዛሬዉ እለት ህዝባዊ እምቢተኝ ተስተዋለ።ፓሊሶች ተደብድበዋል።ፖሊሶች ተጎድተዋል። የመንግስት ታጣቂ ሐይላት ክላሽ ኢንኮቫቸዉን ተቀምተዋል።

መንግስት ያወጣዉን የመሬት ይዞታ አዋጅ በመቃወም ዛሬ በድንገት የተደረገዉ ሰልፍ ፖሊሶች ህዝቡን መቆጣጠር ተስኖአቸዉ በህዝብ ቁጥጥር ስር የዋሉበት አጋጣሚ እንደነበር የሰልፉ ታዳሚዎች ያስረዳሉ። መንግስት ከአያት ቅድመ አያቶቻችን የወረስነዉን መሬት እየቀማ ለኢንቨስተሮች ይሰጥብናል የሚሉት የቡታጅራና የአካባቢዉ ነዋሪዎች ተወልደን ባደግነበት ቀዬ እንድንፈናቀል ተደርገናል ሲሉ ቅሬታን ያሰማሉ።

የአካባቢዉ ነዋሪዎች ለቢቢኤን እንደገለጹት ልክ የአዲስ አበባዉን የሚመስል ማስተር ፕላን በድብቅ ተሰርቶ ስራ ላይ እየዋለ ነዉ። በህወሃት የሚመራዉ መንግስት የመስቃንን ማህበረሰብ መሬት በተቀናጀ መልኩ ለመዝረፍና ጥቅሙን ለሚያስከብሩ አካላት ለመስጠት የምስጢር ፕላኑን ወደ መሬት ላይ ለማዉረድ ሲሞክር ነዉ ዛሬ በፖሊሶችና በህዝብ መካከል ግጭት የተነሳዉ።

የተቦን፣ዊጣ፣ወዶ፣ጆሌ ሐሙስ ገበያ በሚባሉት የመስቃን ወረዳ ቀበሌ ገበሬ ማህበራት ያሉ አርሶ አደሮች መሬታቸዉ እየተቀማ ህወሃት መራሹ መንግስት ለሚፈልጋቸዉ አካላቶች መሰጠቱን የሚያስረዱት አርሶ አደረሮች ጉዳዩ የህልዉና ጉዳይ ስለሆነ ለአቤቱታ ወደ ቡታጅራ ከተማ በመጡበት መታሰራቸዉን ይገልጻሉ።

በገዛ መሬታቸዉ ቤት የሰሩ አርሶ አድረሮች ከተማዎች በሚስፋፉበት ወቅት ቤቶቻቸዉ እንደሚፈርሱ በምሬት ይናገራሉ።እንደ ቅርስ የያዙት ቤትና ንብረት እንደመከነ የሚገልጹት አርሶ አደሮች ከከተማ ራቅ ወዳሉ የገጠር ቀበሌዎች የመሰቃን ወረዳ እና የቡታጀራ ከተማ አሰተዳደር ባለስልጣናት ከታጣቂ አጃቢዎች ጋር በመጓዝ የገጠር ቤቶች ከመንግስት ፍቃድ ዉጪ የተሰሩ በመሆናቸዉ መፍረስ አለባቸዉ ቤቶቹን ለማፍረስ ያደረጉት ሙከራ በዉርደት መጠናቀቁን ነዋሪዎቹ ለቢቢኤን ገልጸዋል።

“እኛ የገጠር ነዋሪዎች ነን፤ በገጠር ዉስጥ ልክ እንደ አያት ቅድመ አያቶቻችን ቤት እንሰራለን፤ ይህንንም ለማድረግ የማንም ፍቃድ አያሻንም!” በማለት ባለ ሰልጣናቱ የታጀብቡበትን ክላሽ-ኢንኮቭ በመንጠቅ ከየቀበሌ ገበሬ ማህበራቱ እንዳባረሯቸዉ የመስቃን ወረዳ ነዋሪዎች ለቢቢኤን ገልጸዋል።

በመሬት ነጠቃዉ የተንገፈገፉ የቡታጅራ ነዋሪዎች በዛሬዉ እለት ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ አደባባይ መዉጣታቸዉን የገለጹልን የቡታጅራ ነዋሪዎች በከተማዋ ዉስጥ እየዞሩ የተቃዉሞ ድምጽ ማሰማታቸዉን ለቢቢኤን ገልጸዋል።ሰላማዊ ሰላፍ አድራጊዎቹ “መንግስት ሌባ፣ ፖሊስ ሌባ፣መብታችን ይከበር፣የታሰሩት ይፍቱ፣ጥያቄያችን ይመለስ!” እያሉ ድምጻቸዉን ሲያሰሙ ከአገር ሽማግሌ በስተቀር ሊያቆማቸዉ የሞከረ የፖሊስ ሐይል አለመኖሩ ለማወቅ ተችሏል።

ተቃዉሞዉ በሚደረግበት ሰዓት ባንክ ቤቶች፣ቤንዚን ማደያዎች፣ሱቆች ምግብ ቤቶች የተዘጉ ሲሆን ከተማዉን ከሆሳእና፣ከአዲስ አበባ እና ከዝዋይ የሚያገናኘዉ ዋና መንገድ ተዘግቶ እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል።ማምሻዉን በደረሰን መረጃ መሰረት ፈዴራል ፖሊስ ከወልቅጤ ከተማ ቡታጅራ ድረስ በመምጣት ሰፍሯል። ዉጥረት ቡታጅራ ዉስጥ ነግሷል። ይህ ዉጥረት ወዴት እንደሚያመራ ባይታወቅም፥ የታወቀዉ ነገር ቢኖር ባልተጠበቀ መልኩ በየተኛዉም የኢትዮጵያ ክፍል ህዝባዊ እምቢተኝነት ሊከሰት እንደሚችል ነዉ። ዛሬ ቡታጅራዎች ይህንን አስመስከረዋል::

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here