የቁቤ ጉዳይ የማይቸግር ለቸገራቸዉ “አፍቃረ – ኢትዮጵያውያን” ከባይሳ ዋቅ -ወያ

0
423

መግቢያ

በቅርብ በኢትዮ ሜድያ ገጾች ላይ ብቅ ካሉት መጣጥፎች ሁለት የኦሮምኛ ቋንቋን በቁቤ መጻፍን አስመልክተው ፊደል፡ ቋንቋ፡ ሕዝብ በተሰኘ አርዕስት በፕሮፈሰር ጌታቸዉ ኃይሌ እና በኦሮምኛ ግዕዝ ፊደላትን ስለመጠቀም ተገቢነት በሚል አርዕስት “አብርሃም ቀጀላ” በተባለ ግለሰብ የተጻፉ በይዘታቸዉ በጣም የተቀራረቡ ሁለት ጽሁፎች ቀልቤን ስለሳቡ አንብቤ ካጣጣምኳቸው በኋላ አልዋጥልህ ስላሉኝ ይህንን ግላዊ አስተያየት በጽሁፍ ለማስፈር ወሰንኩ። ኦሮሞ-ኢትዮጵያዊ በመሆኔ ደግሞ ጉዳዩ ከማንም በላይ ያገባኛል የሚል ግምትም አለኝ። አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል የሚባለው ሆኖብኝ ነዉ። እኔ ግን አፍንጫዬን ሳይሆን ዓይኔን የተመታሁ ያህል ስለተሰማኝ በተቻለ መጠን ስሜቴን ተቆጣጥሬ ትርፍ ቃላትም ሳልጠቀም ወግና ባህሉ በሚፈቅደው መሰረት “እስዎ” “እናንተ” እያልኩ እቀጥላለሁና ከኔ ጋር ይቆዩ። ለመንደርደርያ ያህል ግን በቅንፍ ውስጥ ለምን መልስ ለመስጠት እንደወሰንኩ ባጭሩ ላስረዳ።

በኔ አስተያየት ምድራችን በምታኖራቸው ሰዎች ልክ የተለያዩ ጠባዮችንና ርዕዮተ ዓለሞችን ታስተናግዳለች። አንዳንዱ ሰው ዝም ብሎ ለክፋት ሳይሆን እንደሁ በማያገባው ነገር እየገባ በማያስጨንቅ ነገር ሁሉ ይጨነቃል፡ “የማይቸግር የቸገረው” የሚሉት ዓይነት ነው። ይህ እንግዲህ ተፈጥሮ ያደለው ጠባይ ስለሆነ መፍትሄውን ለግዜር መተው ነው። ሌላው ደግሞ እውኔታውን እያወቀ ለተንኮል ብቻ ሲል ነገሮችን በአሉታዊ መልኩ ብቻ የሚያይ አለ፡ “አውቆ የተኛ” የሚባለው መሆኑ ነው። አንዳንዱ ደግሞ የዚህ ታቃራኒ የሆነና ለክፋት ብሎ ሳይሆን ለአንድ በአዕምሮው ውስጥ አስቀድሞ ለቀረጸው ትልቅ ዓላማ መሳካት ሲል ከዚህ ከዓላማው ጋር የማይገጥመውን ሃሳብ ሁሉ ጎጂ አርጎ በማየት ውድቅ የሚያደርግ ነው። እንደኔ ግምት ፕሮፈሰር ጌታቸዉ ኃይሌ እና “አብርሃም ቀጀላ” በዚህ በመጨረሻ ላይ በጠቀስኳቸው ግለሰቦች ቡድን ተርታ ይመደባሉ ባይ ነኝ። ለዚህም ነው እኔም በየዋህነት የነሱንም አስተሳሰብ በቅንነት ስለወሰድኩ ይህንን መልስ ቢጤ ለመጻፍ የወሰንኩኩት። ፕሮፈሰርና አቶ አብርሃም እንድትረዱልኝ የምፈልገው ግን – ዓላማዬ እናንተን “ለማጋለጥ” ሳይሆን እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ላገሪቷና ለህዝቧ በጎ ከማሰብ የጻፋችሁ ነው ብዬ ስለምገምት ከዳር ቆመው እሰዬው በለው፡ ልክ ልኩን ንገረው እስከ ዶቃ ማሰርያው ድረስ …” በሚሉ ወገኖችም ሳልዋከብ በተቻለ መጠን ሚዛናዊ የሆነ የግል አስተሳሰቤን ለማስፈር እሞክራለሁ። ለሁለታችሁም የተለያየ ጽሁፍ በመጻፍ የአንባቢዎችን ጊዜ ከማባከን ደግሞ በዚሁ ባንድ መልዕክት ጠቅለል አድርጌ ለማለት የፈለግሁትን ለማስተላለፍ ወስኛለሁ። ሁለት ወፎችን ባንድ ድንጋይ እንደሚሉት መሆኑ ነዉ። እንቀጥል።

ከወዲሁ ግን በቅንፍ ውስጥ አቶ አብርሃምን ለማለት የምፈልገው አለኝ፡ ከየትኛው ብሄር እንደሆኑ በትክክል መናገር ባልችልም ኦሮሞ አለመሆንዎን በርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡ ሳስበው ኦሮሞ መስለው የቁቤን “ጉድለት” መጻፍ “ይሄው – ኦሮሞዎች ራሳቸው “ቁቤ ጎጂ መሆኑን ይጽፋሉ” ለማሰኘት ምንጩ ከየት እንደሆነ የማይታወቅ “ቀጀላ” የሚል ያባት ስም መጠቀምዎ ገዢ የሚያስገኝልዎት መስሎዎት ከሆነ በጣም ተሳስተዋል። ከሩብ ምዕት ዓመት ልምምድ በኋላ ግን ”ቃጄላ“ ን በትክክል መጻፍ አለመቻል ትዝብት ያስከትላልና ያስቡበት ባይ ነኝ።

ዋናው ጉዳይ

ወደ ዋናው ጉዳይ ልመለስና ቢያንስ ቢያንስ ከሩብ ምዕት ዓመት በፊት አላስፈላጊ የሆነ ሙግት ከሁሉም አቅጣጫ ተከፍቶበት ከሞላ ጎደል ዕልባት ያገኘውን ጉዳይ ዛሬ በሀገራችን ላይ በታሪኳ ሙሉ ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅበት ደረጃ የዜጎቿ መብቶች እየተረገጡ፡ ሕጻናትና አሮጊት በአደባባይ እየተረሽኑ፡ ሌሎች ደግሞ ማዕከላዊ ተወርውረው አቶ ሀብታሙ አያሌው እንዳሉት “በህይወት ከመኖር ይልቅ ሞትን በሚመርጡበት ሰዓት” በቁቤ ጉዳይ ላይ ጊዜ ማጥፋት የሚያሳስብም የሚያናድድም ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም። እስከማስታውሰው ድረስ እነዚህ ግለሰቦች ወያኔ በመፈጸም ላይ ያለውን በስፋቱም በጥልቀቱም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ዘርና ወገን ሳይለይ የሚያካህደውን ጭፍጨፋ በመኰነን የጻፉት ነገር ትዝ አይለኝም። አቶ አብርሃምን አላስታውስም እንጂ ፕሮፈሰር ኃይሌንማ ስለ ኦሮሞ ሕዝብ በተለይም ስለ ቋንቋው ከኔ በላይ አዋቂም ተቆርቋሪም ላሳር ነው የሚሉ “ለኢትዮጵያ አንድነት” ዘብ የቆሙ አንጋፋ ዘበኛ መሆናቸውን ከሌሎች ጽሁፎቻቸው ለመረዳት ችያለሁ። (በነገራችን ላይ ቁቤ በእንግሊዝኛ phonetic የሚሉት ሲሆን የላቲን ፊደል ደግሞ ለኦሮምኛ ቋንቋ ማሳደጊያ የተዋስነው ነው።

ለሁለቱ ግለሰቦች መልስ መስጠት የፈለግሁት በሁለት ዐብይ ምክንያቶች ነው። አንደኛው፡ ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላ እነዚህ አማርኛ ተናጋሪ ምሁራን ውድ ጊዜአቸውን ሰውተው የኦሮምኛን በላቲን ፊደል መጻፍ አሉታዊ ጎን ማለትም ለ“ኢትዮጵያ አንድነት” ጠንቅ መሆኑ ለነሱ ብቻ የታያቸው አንድ መለኮታዊ የሆነ ግን ለኛ መንገር ያልፈለጉት ምሥጢር ይኖራል ብዬ በማሰብ ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ያገራችን ሕዝብ እንደሁ ፈርዶበት በፕሮፈሰር የተጻፈ ሁሉ ትክክል ነው ብሎ ስለሚያምን ለነዚህ ቅን ወገኖች የቁቤው ተጠቃሚ ምሁራን በበኩላቸው ምን እንደሚያስቡ መልዕክት ለማስተላለፍ ነው። አለያማ ገና ከመጀመርያው በዘጠናዎቹ መጀመርያ አካባቢ ገና ቁቤ ዳዴ ሳይል በጨቅላነቱ ለመቅጨት አማርኛ ተናጋሪ ምሁራን ብቻ ሳይሆኑ አብያተ ክርስትያናት እንኳ ሳይቀር ተደማምረው በኦሮምያ ክልል የሚገኙት ቄሳውስት በየእሁዱ ስብከት እያስታከኩ ቁቤ የሰይጣን ፊደል ስለሆነ በሱ የተጻፈውን መጽሃፍ ቅዱስ እንዳታነቡ ውግዝ ከመዓርዮስ” “ይህንን ውግዝ ጥሳችሁ የተገኛችሁ ሴቶች ጥቁር ውሻ ትወልዳላችሁ፡ ወንዶች ደግሞ እንደ ሳጥናኤል ቀንድ ታበቅላላችሁ እያሉ ላንቃቸው እስኪሰነጠቅ ድረስ ያውጁ ነበር፡፡ በኦሮምያ ክልል ብዙ ታቦቶች ለጥምቀት ወጥተው “ቁቤ ካገር ካልጠፋ ተመልሰን አንገባም”  ብለው ኦሮሞ ምዕመናንን ያስቸግሩ እንደነበር ሁላችንም ታዝበን ያለፍነው ክስተት ነበር። አንድ በአምቦ አካባቢ የሚገኝ የሚካኤል ታቦት ለጥምቀት ወጥቶ “ቁቤ የሚባል ነገር ካገር ካልጠፋ ተመልሼ አልገባም” ብሎ ባለበት ሲቆም ፀሃዩ በጣም ያቃጠላቸውና ድሮም ቢሆን ለጉግስ እንጂ ለጥምቀቱ ብዙም ዴንታ ያልነበራቸው የአምቦ ጎረምሶች ሚካኤል ትገባ እንደሁ ግባ አለበለዚያ እኛ እዚህ ቆመን በፀሃይ የምንንቃቃበት ምክንያት አይታየንም ብለው ወደ ጉግስ ጨዋታቸው ሄዱ ብሎ አንድ የአምቦ ጓደኛዬ ያጫወተኝ ቀልድ ትዝ አለኝ።

ዛሬ ቁቤ በግሩ መሄድ ብቻ ሳይሆን ጎልምሶ ራሱን በራሱ ሊያስተዳድር የሚችል አባወራ ሆኖአል። የኦሮሞ ህዝብም ቁቤን በጉዲፋቻ ከወሰደው በኋላ በባህሉ መሰረት ከአብራካቸው እንደወጣ በመቁጠር እየተንከባከቡት ሲሆን ቁቤም የኦሮሞን ህዝብ እንደ እውነተኛ ወላጆቹ ተቀብሎ በተድላና ደስታ እየኖረ ነው። ይህ እንግዲህ በእኛ በኦሮሞዎች ዓይን የሚታይ ዕውነታ ሲሆን ከላይ እንዳልኩት አንዳንድ አማርኛ ተናጋሪ የቋንቋ ሊቃውንት ነን ባዮች ደግሞ ሌላ ለኦሮሞዎች የማይታይ ለነሱ ብቻ የሚታያቸው የላቲንን ፊደል ለኦሮምኛ ጎጂ እንደሆነ አርገው የሚያቀርቡት ነገር አላቸው።

እውነቱን ለመናገር – ይህ በቁቤ ዙርያ የሚካሄደው ክርክር እንደሁ ለመልስም የማይመች ነገር እየሆነብኝ ሄዶአል፡ ምክንያቱም ፀረ ቁቤዎቹ የሚያነሷቸው ነጥቦች አንዳቸውም ወይ በሳይንስ የተደገፈ አለያም ያገሪቷን ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ የሚያንጸባርቅ ተጨባጭ  ማስረጃ ሳይሆን ይዘው የሚመጡት እንደሁ በደፈናው “ያገሪቷ አንድነት” በሚል ይዘቱ ግን በግልጽ የማይነገር የማይብራራ መለኮታዊ አባባልን ነው። ደፍረው ደግሞ በጽሁፍ ካስቀመጡ የሚያቀርቧቸው ነጥቦች ከጭፍን ስሜታዊነት የማይዘሉና ባብዛኛው ትክክል ያልሆኑ ጨብጦች ናቸው። የኦሮሞዎች የላቲንን ፊደል ተውሰው መጠቀሚያ ማድረጋቸው የሌሎቹን ብሄር ብሄረ ሰቦች መብት ተጋፍቷል ቢባል ኖሮ አግባብ ያለው ሙግት ነው። ምክንያቱም የአንደኛው ወገን መብት መከበር የሌላውን መብት መጣስ  ተገቢ አይደለምና! ያ ከሆነ ደግሞ ለሰው ልጅ መብት መቆርቆር በምድራዊው ሕግም ሆነ በግዜር ፊት የሚያስከብር ስራ ነውና ሙግቱን ተገቢ ያደርገው ነበር። በኦሮሞዎች የላቲን ፊደል መጠቀም በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የአንድን ግለሰብ የአንድን ብሄር/ብሄረሰብ ወይም የሕዝቦችን መብት ተጋፍቷል የሚል ውል ያለው አንዲት ነጥብ እንኳ ሳያቀርቡ እንደው ዝም ብለው “ለኢትዮጵያ አንድነት” የሚል ቅርጸ – ቢስና ሰንካላ ምክንያት እያነሱ በነጋ በጠባ መወትወት “ቀበሮ ሊበላኝ” ነው እያለ በውሸት ወላጆቹን ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ሲያስጨንቅ እንደነበረው ልጅ አንድ ቀን የውነት ቀበሮ ሊበላው ሲመጣ ወላጆቹ “ያው እንደተለመደው” ብለው ሳይደርሱለት ቀርተው እንደተበላው ልጅ የመሆን ያህል ነው። የሰው ልጅ መብት ለሰው ልጆች ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ ግዑዝ ምድር ስለሆነች የሰው ልጆች መብት ተጠቃሚ አይደለችም አይመለከታትም። ስለዚህ የምናወራው ስለ ሰው ልጆች መብት (ብሄሮች የሰው ስብስብ ናቸውና) እስከሆነ ድረስ ደግሞ ግዑዝ መሬትንና ነፍስ ያለውን ሕዝብ አንድ ላይ ጠቅልሎ ለሙግት ማቅረብ ስህተት ይመስለኛል።

“ያገሪቷ አንድነትን” በተመለከተ ዝቅ ብዬ በዝርዝር ስለምመለስበት ስሜታዊና ትክክል ያልሆኑ ጨብጦች ያልኩብትን ምክንያት እስቲ ባጭሩ ላስረዳ። ለምሳሌ ያህል አቶ አብርሃም ከላይ በጠቀስኩት ጽሁፋቸው እንድህ ይላሉ፡

በእነዚህና በመሳሰሉት ብዙዎች ሁሉ ተፈትሾና ተፈትኖ ብቃቱ የተመሰከረለት ሁኖ ስላለና በተጨማሪም በተላያዩ አገራዊና ዓለማዊ በከፍተኛ ደረጃ የቋንቋ ምሁራንና የቋንቋ ሳይንቲስቶች በተደረጉ ጥናቶች የግእዝ ፊደል ያለድርቦሽ ወይም ያለጥንድ ደባል ፊደል ወይንም ያለመንታ ፊደል በነጠላው ድምጽ ባለቤትነት በሚገባ የሚያገለግል ጥናታዊ ፊደል መሆኑ ተረጋግጧል” (ስርዝ የኔ)

በኔ ግምት ይህ ትክክለኛ አባባል አይመስለኝም። በመጀመርያ ደረጃ አገራዊና ዓለማዊ …….. ሳይንትስቶች የመሰከሩለት ከሆነ ማስረጃውም አብሮ ቢቀርብ ጥሩ ነበር። በኔ ግምት ግን የግዕዝ ፊደል በነጠላው ድምጽ ባለቤትነት እንኳን የኦሮምኛን ቋንቋ ይቅርና የአማርኛን ቋንቋ እንኳ በሚገባ አያገለግልም ባይ ነኝ። እስቲ አቶ አብርሃም የሚቀጥሉትን ለናሙና ያህል ያቀረብኳቸውን የአማርኛ ቃላት በጽሁፍ ሳስቅምጥና ዓረፈተ ነገር ውስጥ ሳይከቷቸው እንድሁ እንዳሉ ምን ለማለት እንደፈለግሁ ይንገሩኝ። ይበላል፦አይበላም፦ የሚበላ የሚጠጣ፡ ይጠጣል፦ አይጠጣም፦ይከሳል፦ ይፈራል፦ አይፈራም፦ ይሰራል፣ አይሰራም፦ ይኖራል፡ እንዳለ።  እነዚህን ከላይ ለምሳሌ ያቀረብኳቸው ቃላት በአረፍተ ነገር ውስጥ ካልተካተቱ በስተቀር ለብቻቸው አሻሚ ትርጉም ነው የሚሰጡት። አንባቢ ትርጉሙን እንዲረዳ ከተፈለገ ሙሉ ዓረፍተ ነገሩ መጻፍ አለበት ማለት ነው። በቁቤ ግን ይህ ችግር መቶ በመቶ ተቀርፎአል። ፊደሎቹ ጥንድ ወይም ደባል ቢሆኑም በቁቤ በተጻፈ ዓረፍተ ነገር ውስጥ በምንም ተዓምር ጣምራ ትርጉም ያለው አንድም ቃል ሊገኝ አይችልም። ይህ እንግዲህ በቅንነት ላስተዋለው ሰው የኦሮምኛን ቋንቋ በላቲን ፊደል መጻፍ አዎንታዊ ጎኖቹ ብቻ እንዳሉት የሚያሳይ ነው።

አቶ አብርሃም ግን በዚህ አላቆሙም ትንሽ ወረድ ብለው;

በሌላ በኩልም በህትመት ጎንዮሽ ጉዳይም በላቲን ፊደል ተጠቅሞ ሲታተም 300 ገጾች የሚፈጅ መጽሐፍ በግእዝ ፊደል ሲታተም 100 ገጽ ብቻ እንደሚፈጅ በናሙና ንጽጽር ጥናቶች በተጨባጭ የመጻሕፍቶቹን ህትመቶች አቅረበው አሰይተዋል።

ይሄ ደግሞ ትንሽም ቢሆን ያስቃል። በመጀመርያ ደረጃ ጥናቶቹና የትና መቼ እንደተካሄዱ እና ውጤቶቹ ምን እንደሆኑ ከጽሁፉ ጋር አብሮ ቢቀርብ ለማሳመን እንኳን ባይሆን ለማደናገር ያመች ነበር። ግን አልሆነም። በርግጥ በቁቤ ሲፃፍ መንታ ፊደላት ስለሚበዙበት ረዘም ያለ ገጾችን ሊወስድ ይችላል። ግን በአማርኛ ሲጻፍ ከሚከሰቱት የብዙዎች ቃላት ጣምራ ትርጉምና ቃሎቹን ለመተርጎም እንዲረዳ ከሚፃፉት ዓረፍተ ነገሮች ብዛት ጋር ሲተያይ በቁቤ የሚጻፈው ኦሮምኛ ትንሽ ገፅ ነው የሚፈጀው። ስለዚህ አቶ አብርሃም ሌላ የሚያሳምን መረጃ ካለዎት ያቅርቡ እንጂ ይሄኛው ብዙም ውሃም አይቋጥርም።

እስቲ ደግሞ ወደ ዋናው እና ዘወትር የሚነሳውን የ “ኢትዮጵያ አንድነት” ጉዳይ በጥልቁ እንመልከት። ከላይ እንዳልኩት ለዚህ ጽሁፌ መነሻ የሆነውን የሁለቱንም ግለሰቦች ጽሁፍ አንድ የሚያደርገው ሁለቱም ኦሮምኛን በላቲን ፊደላት መጻፍ ለኢትዮጵያ አንድነት ፀር ነዉ የሚል አቋም ማስተጋባታቸው ነው። ለዚህ አባባላቸው ዋቢ አርገው የሚያቀርቡት ሳይንሳዊ ጥናት ስለሌለ እንድሁ በደፈናው “አንድ አገር ፡ አንድ ቋንቋ፡ አንድ ፊደል” የሚለውን ቅርጽና ይዘት-የለሹን ከአንድ ምዕት-ዓመት በላይ ሲያደነቁረን የኖረውን አደዳቢ መፈክር መነሻ ያደረገ ነው ብል ከዕውነት የራቀ እንደማይሆን አምናለሁ።

ፕሮፈሰር ጌታቸዉ በጽሁፋቸው ውስጥ በትክክል እንዳስቀመጡት

”…… ሌሎቹ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በገበያ ላይ ካሉት ፊደሎች የትኛውንም ፊደል መርጠው ሊወስዱ ይችላሉ። ግን በሚወሰድበት ጊዜ፥ እንኳን ፊደልን ያህል ትልቅ ነገር ቀርቶ፥ ነገ አርጅቶ የሚጣል ዕቃ እንኳን የሚገዛው አማርጦ፥ አገላብጦ አይቶ፥ ይበልጥ የሚስማማ የመሰለው ተመርጦ ነው።

አባባሉ እጅግ በጣም ትክክለኛ ስለሆነ ተጨማሪ ማብራርያ የሚያስፈልገው አይመስለኝም። ለዚህም ነው የኦሮሞ የቋንቋ ለቃውንትና ሌሎች ምሁራን የላቲንን ፊደላት የተዋሱት ከሌሎቹ በአካባቢያችንም ሆነ ራቅ ብለው ያሉትን ቋንቋዎች አወዳድረው አገላብጠው አይተው ይበልጥ የሚስማማ መሆኑን ካመኑበት በኋላ ነው፡፡ ልክ ፕሮፈሰር ጌታቸዉ እንዳሉት ማለት ነው! ምርጥ አባባል!

ችግሩ የሚመጣው ፕሮፈሰር ወደ ኋላ በሰነዘሩት ቁርጠኛ ሃሳብና ትዕዛዝ መሰል አነጋገር ላይ ነው። አንድ አገር አንድ ፊደል። በሰማንያ ጎሳ ላይ ሰማንያ ፊደል ማምጣት፥ ለሀገራችንበእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሆናል”  ያሉትን ካጤንነው ማለቴ ነው። እንደሁ ወደዚያ “አንድ አገር – አንድ ፊደል” ጉዳይ ከመዝለቃችን በፊት ፕሮፈሰር ጌታቸዉን አንድ ጥያቄ ለመጠየቅ ጓጓሁ። ፕሮፈሰር – እንደው ሲያስቡት የኦሮሞ ሊቃውንት የላቲንን ፊደላት ለመዋስ ሲወስኑ “አማርጦ አገላብጦ ይበልጥ የሚስማማ” መሆኑን ለመገምገም በቂ ዕውቀትና ችሎታ አልነበራቸውም ነው የሚሉን ወይስ ምሁራኑ ሆን ብለው የራሳቸውን ብሄር ማለትም የኦሮሞን ህዝብ ለመጉዳት ብለው ለኦሮምኛ ቋንቋ የማይስማማ ፊደል የተዋሱ ይመስልዎታል?

በርግጥ የአንድ ብሄር ሊቃውንት ቋንቋቸውን ለማሳደግ በግድ ከሌላ ቦታ መዋስ ካለባቸው በመጀመሪያ ደረጃ “ማማረጡንና ማገላበጡን” መጀመር ያለባቸው ከጎረቤት ነው። በተለይ በቋንቋ ተመሳሳይ የሆነ ወይም በነገድ ቅርበት ያላቸው ሕዝብ ባካባቢው ካሉ የነሱን ፊደላት በመጀመርያ ደረጃ መፈተሹ አግባብ ያለው አሰራር ነው። አማርኛ ተናጋሪ ምሁራንም ለአማርኛ ቋንቋ ማሳደጊያ ፊደላት ለመሸመት ባህር ማዶ መሄድ አልነበረባቸውም። እዚያው በቅርብ ካለው ቤት ዘመድ ከሆነው ከሳባውያን መዋስ ነበረባቸው። ሁለቱም ብሄሮች ከሴም ነገድ ስለሆኑ ከዚህ የተሻለ ዕቃ የትም የቋንቋ ገበያ ላይ ሊያገኙ አይችሉም ነበር። አግባብ ያለው ውሳኔ!

ፕሮፈሰር እንደሚሉን ከሆነ በአንድ አገር ውስጥ በተለያየ ፊደል መጠቀም ላገር አንድነት አይበጅም። እንደው ፕሮፈሰር አሁን ማ ይሙት በውነት “የኢትዮጵያ አንድነት” ጉዳይ ያን ይህል ከልብ አሳስብዎት ዕንቅልፍ ነስቶዎት ነው ወይስ ሌላ የተደበቀ ነገር ከኋላ ስላለ ነው? የኦሮሞ ሕዝብ በላቲን ፊደል መጠቀም ከጀመረ ይሄው ሩብ ምዕተ ዓመት አስቆጥሮአል። በዚህ በታሪክ የጊዜ መስፈርት ሲታይ ያን ያህል ረጅም ነው እንኳ ባይባልም አጭር ባልሆነ ጊዜ ውስጥ የኦሮሞ ህዝብ በላቲን ፊደል በመጠቀሙ ላንዲት ደቂቃ እንኳ የኢትዮጵያ አንድነት ለአደጋ መጋለጥ ቀርቶ ጥያቄ ውስጥ የገባበት ጊዜ አልነበረም። ታዲያ ውድ ፕሮፈሰራችን በነጋ በጠባ “ቁቤ ቁቤ” እያሉ ራስዎ እንቅልፍ አጥተው እኛን ዕረፍት የሚነሱን ለስዎ ብቻ የታየና ከኛ የተደበቀ ምን ተአምር ቢኖር ነው?  ለኢትዮጵያ “የህዝቦች አንድነት” ሳይሆን “የግዛት አንድነት” ተብሎ “አንድ አገር – አንድ ቋንቋ – አንድ ፊደል” በሚል መርህ ስር ከአንድ ምዕት ዓመት በላይ በተግባር ላይ የዋለ ኦሮሞዎችና ሌሎች አማርኛ ተናጋሪ ያልሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ቋንቋና ባህሉን እንዳይለማመድ አማርኛን ብቻ በግድ እንዲያውቅ የተደረገበትና በእኩልነት ላይ ያልተመሰረተ የግፍ ሥርዓት ነበር ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ ይህን ስርዓት ነው እንግዲህ ውድ ፕሮፈሰር ውስጡ ሬት የሆነውን ውጪውን ማር ቀብተው ይጣፍጣልና ላሱት የሚሉን። ፕሮፈሰር ኃይሌና አቶ አብርሃም ግን የተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በተለያዩ ፊደላት ከተጻፉ ያገሪቷን አንድነት መሰረት ያናጋሉ ባይ ናቸው። እስቲ ለማብራራት እንዲያመች ነገሮቹን ለሁለት ከፍለን እንያቸው።

በመጀመርያ ደረጃ የምናወራው ስለ አንድ አሃዳዊ አገር ሳይሆን የብዙ ብሄርና ብሄረሰቦች አገር ስለሆነችዋ ኢትዮጵያ ነው። ስለዚህ ስለ ኢትዮጵያ “የግዛት አንድነት” ስናወራ እነዚህ ብሄር ብሄረሰቦች ቋንቋና ባህላቸውን እንደተመቻቸው የሚያሳድጉባት ያንዱ ብሄር ቋንቋ ፊደል ከሌላው ብሄር ቋንቋ ፊደል የተሻለ ነው ተብሎ የማይወሰድበት የእኩሎች አገር ማለት ነው። አባባሌን ለመቋጨት ያህል ስሌቱ እንደሚከተለው ይሆናል፡ የኢትዮጵያ ”የግዛት አንድነት“ ዕውን ሊሆን የሚችለው ”የሕዝቦቿ አንድነት“ ከተጠበቀ ብቻ ነው፡ ”የሕዝቦቿ አንድነት“ ደግሞ የሚገኘው በመካከላቸው በሁሉም ዘርፍ ፍጹም እኩልነት ሲኖር ነው። ውይይታችን ፊደልን በመዋስ ዙርያ ስለሆነ ይህ ”እኩልነት“ በተግባር ሲመነዘር ደግሞ እያንዳንዱ ብሄር ወይም ብሄረ ሰብ ለቋንቋው ዕድገት የሚያመቸውን ፊደል ያለምንም የውጪ ተጽዕኖ መርጦ መጠቀም መቻል ማለት ነው። ሌላ ምንም የሚያወያይ ወይም የሚያከራክር አሻሚ ትርጉም የለውም።

ሁለተኛ ይሄን ዛሬ የፕሮፈሰርና የአቶ አብርሃም ራስ ምታት ሆኖባቸው ዕንቅልፍ የነሳቸው ጉዳይ ከአንድ ምዕት ዓመት በላይ የሞከርነውና ”የኖርነው“ በምንም መልኩ በህዝቦች መካከል ፍቅርና እኩልነትን ሊመሰርት ያልቻለ ኋላ ቀር የሆነ ስርዓት በመሆኑ ተባብረን ከግንዱ ገርስሰን የጣልነው ጉዳይ ነው። በሠንጋ ተራ ቋንቋ ”የተበላ ዕድር“ የሚሉት ዓይነት ነው። ወይም የተሄደበት መንገድ! “በኢትዮጵያ አንድነት” ስም የኢትዮጵያ ህዝቦች በአንድ ቅርጫት ውስጥ ታጉረው “አንድ ናችሁ” ተብለው “በአንድ ግዛት” ውስጥ ኖሩ እንጂ “አንድ ህዝብ” አልነበሩም። የተፈጥሮ ሂደቱን ተከትለው ወደ አንድነት እንዳያመሩ እንኳ ሥርዓቱ የመከፋፈል እንጂ የማዋሃድ ባህርይ ስላልነበረው የታሰበው ህልማዊው “የህዝቦች አንድነት” ሊፈጠር አልቻለም። ጆርጅ ኦርዌልን ኮረጅክ አትበሉኝና በቀላል ምሳሌ ለማስረዳት ልሞክር። የነበረው ሥርዓት – ሙዝ ትርንጎ ሎሚ ብርቱካን ፓፓያ ማንጎ መንደሪን አናናስ እና ለሎች ፍራፍሬዎችን በአንድ ዘምቢል ውስጥ አስቀመጣቸውና “ሁላችሁም ፍራፍሬዎች ስለሆናችሁ አንድ ዘር ናችሁ፡ ከናንተ መሃል ግን ብርቱካን ከሁላችሁም የተሻለ ጣዕም ስላለው ሁላችሁም የብርቱካን ጣዕም የተሻለ መሆኑን ተቀብላችሁ ብርቱካን ብርቱካን መሽተት አለባችሁ፡ ግን ደግሞ ፍራፍሬዎች ስለሆናችሁ በዚህ በጋራ ቅርጫታችሁ ውስጥ በአንድነት በሰላም ኑሩ” ተብሎ ተወሰነባቸው። ከጊዜ ብዛት እንድያውም አንዳንድ ፍራፍሬዎች በተለያየ ምክንያት የራሳቸውን ተፈጥሮአዊ ጣዕም መለወጥ እንደማይችሉ እያወቁ ብርቱካን ብርቱካን እንሸታለን ማለት ጀመሩ። አንዳንዶች ደግሞ በግድ የብርቱካን ጣዕም ነው ያላችሁ ተብለው እንዲያምኑ ተገደዱ። ማታ ማታ ግን ሁሉም በሩን ዘግቶ የየራሱን ዕውነተኛ ሽታና ጣዕም ሲያጣጥም ኖረ። አንድ ቀን እኔም እንደ አንድ ፍራፍሬ ተፈጥሮ ያደለኝ የራሴ የሆነ ጣዕምና ጠረን እንዳለኝ ታውቆልኝ ከብርቱካን እኩል ተከብሬ የምኖርበት ጊዜ ይመጣል ብለው መኖር ቀጠሉ። ታሪክም የራሱን ጊዜ ጠብቆ በራሱ ቀን ዘንቢሉን ዘርግፎ ካሁን በኋላ በግድ ብርቱካን ብርቱካን መሽተት የለባችሁም – እያንዳንዳችሁ የየራሳችሁን ቃና ይዛችሁ በእኩልነት በዘንቢሉ ውስጥ በፈቃደኝነት መኖር ትችላላችሁ ብሎ ፍርድ ሰጠ።

የሚያሳዝነው ግን ያ ሁሉ ጊዜ ካለፈ በኋላ ዛሬ ፕሮፈሰርና ኃይሌና አቶ አብርሃም በርግጥ ሁላችሁም የየራሳችሁ ጣዕምና ቃና አላችሁ፡ ሆኖም ግን እያዳንዳችሁ የየራሳችሁን ቃና መሽተት ከጀመራችሁ ዘምቢሉ መፈራረሱ ነውና ለዘምቢሉ ህልውና ሲባል ሁላችሁም ብርቱካን ብርቱካን እንደሸተታችሁ ቀጥሉ ይሉናል። ለዚህም ምክር – መሰል ትዕዛዛቸው የሚሰጡት በሳይንስ ወይም በሃቅ ላይ የተመሰረተ ሃሳብ ሳይሆን እንድሁ በደፈናው “ለኢትዮጵያም የሚበጃትንም ሆነ ለእናንተ ህልውና እኛ እናውቅላችኋለን” የሚለውን የተለመደ አደዳቢ ስብከት ተመርኩዘው ነው። ያኔ በደጉ ዘመን ይላሉ አበው ላለፈው የተሻለ ሕይወት አምሮታቸውን ሲገልጹ። ዛሬ እንደዚህ የማንም ደብተራና የመንደር ጠባብ ብሄርተኛ መጫወቻ ሳይሆን የብሄርና ብሄረሰቦች ጥያቄ ያኔማ የዲሞክራሲና የነጻነት ፈር-ቀዳጅ የነበሩት የተማሪው ማህበር አባላት ቅንነት በተሞላበት መንፈስ ሳይንስን አስደግፈው የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እንዴት ይጻፉ ብለው ሰፊ የሆነ ውይይት ያካሄዱበት የነበረ ከበሬታ ያለው ጉዳይ ነበር። ፕሮፈሰር “የኢትዮጵያ አንድነት” የሚሉት እንግዲህ ይህን ይመስል ነበር። ከሰማንያ የሚበልጡ የተለያየ ቋንቋና ባህል የያዘውን ህዝብ በአንድ “ኢትዮጵያ በምትባል ዘንቢል ውስጥ አፍኖ ካሁን በኋላ ለኢትዮጵያ አንድነት ሲባል ሁላችሁም የአማርኛ ተነጋሪውን ፊደል ባህልና ቋንቋ እንደራሳችሁ አርጋችሁ ኑሩ ነው የሚሉን እኮ። እኛ ደግሞ “ይሄማ ካንድ ምዕተ ዓመት በላይ ሞክረነው አንገፍግፎን የተውነው ስርዓት ስለሆነ በጭራሽ ወደዚያ አንመለስም ባዮች ነን። ባፍንጫችን ይውጣ እያልን ነው።

አቶ አብርሃም እና ሌሎች የቁቤ ጠላቶች የኦሮምኛን በቁቤን መጻፍ ከፖለቲካ ጋር ያያይዙትና በሻቢያ ግፊትና በወያኔ አግባቢነት ኦነግ ወስዶት ስራ ላይ ያዋለው የጸረ ኢትዮጵያ አንድነት ማራመጃ ስውር ደባ ነው ብለው ያስቀምጡታል። ነገሮችን ሁሉ የሚያይዙት ከደርግ መውደቅ ከወያኔ ስልጣን መውሰድና በሕገ መንግስቱ ውስጥ የአንቀጽ 39 መካተት ጋር የተያያዘ አርገው ነው። አቶ አብርሃም እንዲህ ይላሉ፡

በሻቢያና በኦጋዴን ነጻ አውጭ እንዲሁም በሶማልያ መንግሥት ይረዳ የነበረው በምስራቅ ደጋ ክልል አካባባቢ ሲንቀሳቀስ የነበረው አቦ ኢስላምያ (ጃራ) የተባለ ወግ አክራሪ ድርጅት አማካኝነትና አባሪ ተባባሪ በመሆን በነዙት ጸረአገራዊነት እና ጸረ አብሮነት ጥቂት የኦነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ በወሰዱት የጥላቻ አቋም ግእዝ ፊደል በላቲን ፊደል እንዲለወጥ ሁኗልይሉናል።ስርዝ የኔ

እውኔታው ግን ሌላ ነው። ኦሮሞዎች የላቲንን ፊደል ለመዋስ የወሰኑት እንደሁ አንድ ቀን ከዕንቅልፋቸው ተነስተው በህልም ታይቶናልና እንዋሰው ወይም ደግሞ ኢትዮጵያን እናፈራርስ ብለው አልነበረም። ታሪኩ ረጅም ነው። ከላይ እንዳልኩት የተውሶውን የሳባውያንን ፊደል ከተዋሱቱ ተውሰን አማርኛ ተናጋሪዎች እንኳ ሳይቀድሙን ተሽቀዳድመን ከመቶ ዓመት በፊት መጽሃፍ ቅዱስን ወደ ኦሮምኛ ተረጎምን። ምንም እንኳ ለማንበብም ሆነ ለመረዳት አስቸጋሪ ሆኖ ብናገኘውም ምርጫ ስለሌለን አንድ ምዕተ ዓመት ሙሉ እንደምንም ተጠቀምንበት። በተለይም ጣምራ አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም ሶስትዮሽ ትርጉም ያላቸውን ቃላት ለመለየት እጅግ በጣም አስቸጋሪ ሆኖ ስላገኘነው ሌላ የተሻለ ፊደል ካለ ብለው የኦሮሞ  ምሁራን ልክ ፕሮፈሰር ኃይሌ እንዳሉት  በ 60 ዎቹ ውስጥ ወደ ፊደላት ገበያ ወጥተው የሚሻለውን ማማረጥ ያዙ። ያኔ በተማሪው ማህበር ይታተሙ በነበሩት “ታጠቅ” እና “ትግላችን” መጽሄቶች ላይም የኢትዮጵያ ምሁራን በሙሉ በጥናት የተደገፈ ማስረጃ እያቀረቡ ገንቢ ውይይቶችን ያካሄዱ ነበር። (የሳባውያን ፊደል ለኦሮምኛ ቋንቋ እንደማይበጅና  በላቲን ፊደል ቢጻፍ የተሻለ መሁኑን ለማስረዳት ያህል ያኔ ይቀርቡ ከነበሩት አንዳንድ ነጥቦች እንደ ኛዴን ዱፌእናቶኮ ዱፉን ዲሩማዳ ላማ ዱፉን ሃሩማዳ”)  ዛሬም ትዝ ይሉኛል። ታድያ የዓለም ገበያ ላይ ከነበሩት ሃያ ከማይሞሉ ፊደላት የላቲኑ ፊደል ከሁሉም በላይ ተስማሚ ሆኖ ስላገኙት በጉዲፋቻ ወሰዱት። የመጀመርያው በላቲን ፊደል የተጻፈው የኦሮምኛ ስዋስው “Hirmaata dubii afaan Oromoo” በፈረንጆች አቆጣጠር በ 1973  ዓመተ ምህረት የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር አባል መሪ በነበሩት በነኃይሌ ፊዳ ተደርሶና ታትሞ  “ህጋዊ ባልሆነ መንገድ” ለጠቀሜታ ዋለ። በዚያን ጊዜ ኦነግም ሆነ አቦ እስላሚያ አልነበሩም አልተፈጠሩምም።

ሕጋዊ ”ባልሆነ መንገድ“ ያልኩበትን ምክንያት ትንሽ ላብራራ መሰለኝ። በዘጠናዎቹ መጀመርያ ላይ ሕጉ ከመሻሻሉ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሳባውያን የዘር ሃረግ ከሚወለደው የግዕዝ ፊደል በስተቀር ሌላን ፊደል በጉዲፋቻ መውሰድ ወንጀል ነበር። ለዚህ ነው ወያኔ ሥልጣን ወስዶ ማንኛውም ብሄር/ብሄረሰብ ከፈለገበት ቦታ የፈለገውን ፊደል በራሱ ምርጫ በጉዲፋቻ መውሰድ ይችላል የሚል መብት የሚያካትት ሕግመንግስት እስኪያውጅ ድረስ ኦሮሞዎች የላቲንን ፊደል ይጠቀሙ የነበሩት “ከሕግ ውጪ” ነበር ያልኩት። በዘጠናዎቹ መጀመርያ ላይ ኦሮሞዎች ለዓመታት በድብቅ ያሳደጉትን የጉዲፋቻ ልጃቸውን (የላቲንን ፊደል) በግልጽ በአደባባይ ማሳየት ጀመሩ እንጂ አቶ አብርሃም እንደሚሉት “ጥቂት የኦነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት” ከሻቢያና ወያኔ ጋር ሸርበው ያመጡት “ጸረ አገራዊና ጸረ አብሮነት”  ሴራ አይደለም። ምናልባት አቶ አብርሃም የኦሮምኛን ቋንቋ በላቲን ተጽፎ በዓይናቸው ያዩት ወያኔ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ከሆነ ከላይ ከጽሁፋቸው ቀንጭቤ የጠቀስኩት በቅንነት የተጻፈ ነው ብዬ አምናለሁ። የአቶ ቃጄላ ልጅ ሆነው ይህን ዕውኔታ በቅጡ አለማወቅ ግን ትንሽ ጥርጣሬ ውስጥ ይከታልና ያስቡበት።

በህገ መንግስቱ ውስጥ አንቀጽ 39 የተካተተውም የብሄሮችን የእኩልነት መብት ለማረጋገጥ ተብሎ ሲሆን ይህም እኩልነት ከተተረጎመባቸው ተግባራት አንዱ ኦሮሞዎች ቋንቋቸውን በላቲን ፊደል ለመጻፍ መወሰናቸው ነው። የኦሮምኛ በላቲን መጻፍ ”ለኢትዮጵያ አንድነት“ ጎጂ ነው ብለው የማይቸግር የቸገራቸው እንደ ፕሮፈሰር ያሉ ግለሰቦች ዕውነትም ዝም ብለው ተጨንቀው ሰውን ያስጨንቃሉ እንጂ አንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝማ ህገ መንግስቱ ውስጥ በመካተቱ እስከዛሬ ድረስ ይሄው ከሩብ ምዕተ ዓመት በኋላ አንድም የኢትዮጵያ ብሄር ህገ መንግስታዊ መብቴ ነው ብሎ በክልሉም ሆነ በፈዴራሉ ፓርላማ የመገንጠል ጥያቄ አላቀረበም። የኦሮሞን ሕዝብ ፍላጎት በተመለከተ ደግሞ የሩብ ምዕተ ዓመቱን ተሞክሮ  እንተውና ላለፉት ሁለት ዓመታት የኦሮሞ ሕዝብ ከዳር እስከዳር በነቂስ ወጥቶ ብሄራዊ መብቴ ይከበርልኝ ብሎ በወያኔ መንግስት ላይ ሲያምጽ አንድም ጊዜ አንድም ቦታ ላይ ከኢትዮጵያ ልገንጠል የሚል መፈክር አንግቦ ኧልታየም። የቁቤ አባቶች እነ ኃይሌ ፊዳም ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ የታገሉትም የሞቱትም መላው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በእኩልነት በሰላምና በመፈቃቀር የሚኖሩባትን ዲሞክራቲክ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ነበር እንጂ ኢትዮጵያን ለመከፋፈል አልነበረም። ፕሮፈሰር በተማሪው እንቅስቃሴ ዘመን ከማን ጋር እንደወገኑ አላውቅም እንጂ ብሩህና ቀና አስተሳሰብ ያላቸው ተማሪዎችና ምሁርማ በሙሉ ባንድ ላይ ተረባርበው ችግሩ የሚፈታበትን መላ ሲመቱ ነበር። ይግባቡበት የነበረው መሰረታዊ ሃሳብ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ሳይሆን በመፈቃቀርና እኩልነት ላይ የተመሰረተ የህዝቦቿ አንድነት ሊፈጠር የሚችለው ብሄሮች የራሳችውን ዕድል በራሳቸው መወሰን ሲችሉ ብቻ ነው የሚል ነበረ።

አውጥተን አውርደን ስናየውይሉናል ፕሮፈሰር “ምርጫው ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች መጻፊያ ከሆነ፥ በብዙ ምክንያት፥ ከኢትዮጵያ ፊደል የተሻለ ፊደል የለም  አቶ አብርሃም ቀበል ያረጉና በርካታ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደረጉ ጥናቶች አሁንም ዛሬ በግእዝ ፊደል መጠቀም ቀላልና ለሕዝብ ሳይኮሎጅካል ማኅበራዊና ብሔራዊ ማግባባት እንደዚሁም ለመጭው ትውልድ አብሮነት ተወዳዳሪና መተኪያ አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑንና ይሄው እንዲፈጸም በበርካታ መረጃዎች እያስደገፉ በማስረዳት ላይ ይገኛሉ” ይሉናል

መጀመርያ ነገር፡ የኢትዮጵያ ቋንቋ ወይም “የኢትዮጵያ ፊደል” ብሎ ነገር የለም። ያለው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ቋንቋና ለጊዜው የሳባውያን እና የላቲን ፊደል ነው። የተሳሳት መረጃ እያቅበልን ህዝቡን ባናሳስት ጥሩ ነው። “ከኢትዮጵያ የተሻለ ፊደል የተሻለ የለም” ሲሉ ምን ለማለት እንደፈለጉ ይገባናል። ላቲን የባዕድ ፊደል ነውና የሳባውያንን ፊደል ምረጡ ነው የሚሉን። የተዋሱበት ጊዜ ይለያይ እንደሁ እንጂ ፕሮፈሰር ሁለቱም ከውጭ አገር በውሰት የመጡ የውጪ ፊደሎች ናቸው። ያው እንደተለመደው “የሚጥምህን እኛ እናውቅልሃለን” ካልተባለ በስተቀር የአንድን ፍሬ ጣዕም የሚያውቀው በልቶ የሚያጣጥመው ነው እንጂ ተመልካቹ ሊሆን እንደማይችል ፕሮፈሰርም በደንብ የሚረዱት መሰለኝ።

መደምደምያ

ውድ ፕሮፈሰር፡ እኔን ይልቅ የሚያሳስበኝ የአማርኛ ቋንቋ በሳባውያን ፊደል መጻፉ ለቋንቋው ዕድገት ትልቅ መሰናክል እየሆነ መሄዱ ነው፡ ምናልባት በጊዜው ትክክለኛ ውሳኔ ኖሮ ይሆናል ግን አሁን በአስተውሎት ከታየ በጣም ብዙ መሻሻልና መስተካከል የሚገባቸው ነገሮች አሉበት፡ እኔ እንደ አንድ ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ ጉዳዩ በቀጥታ ባይመለከተኝም እንደሁ በልጅነቴ ብዙ መከራና ሥቃይ ያሳለፍኩበትና በመጨረሻም በስንት ችግር ጠንቅቄ ለማወቅ የቻልኩትን ቋንቋ ዛሬ እንደ አንድ ምሁር ቋንቋውን አሽመድምዶ ይዞ ወደ ኋላ የሚጎትተውን ደካማ ጎኑን ከዳር ቆሜ እያየሁ ለማሳሰብ ከሰነፍኩማ እነ መምህር ጽጌና መምህር ዓባይነህ እጃቸው አመድ አፋሽ ሆነ ማለትነው። አማርኛ ምንም እንኳ የፍልስፍና ወይም የሳይንስ ፋና ወጊ ቋንቋ ባይሆንም እንድሁ በመለስተኛም ደረጃ ቢሆን የተናጋሪውን ህዝብ ፍላጎትና ስሜት ለመጠበቅ እንኳ ሲባል ስር ነቀል የሆነ መሻሻል ያስፈልገዋል ባይ ነኝ። ይሄ የራሳችን ቋንቋ -የራሳችን ፊደል“ እያሉ ራስዎንም ሆነ ህዝቡንም ሃቅ ላይ ባልተመሰረተ ታሪክ ቢጤ ነገር ማደናገር ትተው አማርኛ የራሱ ፊደል እንደሌለውና ካሳባውያን (ባልሳሳት አረቦች ናቸው) ተውሰውትና አሻሽለው ለአማርኛ ፊደል እንደሚጠቅም አርገው ስራ ላይ ያዋሉት በጅምሩ ጥሩ የነበረና ዛሬ ግን ትልቅ መሻሻል የሚያስፈልገው መሆኑን ለተጠቃሚው ህዝብ መንገር አለብዎት። ስለዚህ ውድ ፕሮፈሰር – እንደሁ በማይቸግር ነገር እየተቸገሩ ሌሎችንም ከሚያስቸግሩ እንደ አንድ የአማርኛ ተናጋሪ ምሁር ከለሎች አማርኛ ተናጋሪ ሊቃውንት ጋር በመሆን የአማርኛን ቋንቋ የአቶ ሃዲስ ዓለማየሁን ፈለግ ተከትለው ለማስተካከል ቢሞክሩ ታሪክ የጣለብዎትን ኃላፊነት በአግባቡ የተወጡት ይመስለኛል። ከስዎ በላይ ጠንቅቄ ባላውቅም የሳባውያን ፊደላት በተለይም የሶስተኛ ሰውነት ግሦች ትርጉም በጣም መሻሻል ከሚያስፈልጋቸው ክፍል አንዱ ነው ባይ ነኝ፡ በአረፍተ ነገር ውስጥ ካልተብራሩ በስተቀር ቃሎቹ  ለብቻ ከተፃፉ አሻሚ ትርጉም ስለሚኖራቸው ችግሩ ግዙፍ ነው። ይህንን ስል አማርኛ የሳባውያንን ፊደል ትቶ የላቲን ፊደል ይዋስ ማለቴ እንዳልሆነ ከወድሁ ለመግለጽ እወዳለሁ። (በነገራችንላይ በላቲን በሚጻፈው የኦሮምኛ ቋንቋ ውስጥ ይህ ችግር ሙሉ በሙሉ ተቀርፎአል)።

ቋንቋ ከተናጋሪው ሕዝብ ተለይቶ የማይታይ የማንነት ጉዳይ ነው። ሕዝብ ማለት ደግሞ የሰዎች ስብስብ ከሆነና የሰው ልጆች ደግሞ ሰው ሆነው በመፈጠራቸው ብቻ በፈጣሪም ሆነ በምድራዊም ሕግ ፊት እኩል ከሆኑ ቋንቋቸውም እንደዚሁ እኩል ናቸው ማለት ነው። በሌላ አነጋገር ቋንቋቸውን ላማሳደግም ሆነ የሚጥማቸውን ፊደል ለመዋስ እኩል መብት አላቸው ማለት ነው። የዚህን ተፈጥሮአዊና ሰብዓዊ መብት ይዘት ጠቅለል ባለ መልኩ እንየው ከተባለ ብሄሮች ለቋንቋቸው ዕድገት ፊደል መዋስ ካስፈለጋቸው ያለ ምንም የውጪ ተፅዕኖ ይበጀናል ያሉትን መዋስ ይችላሉ ማለት ነው። ዛሬ ቁቤ ህያው ሆኖአል፡ ሕዝቡም በወሰደው ትክክለኛና ቁርጠኛ ውሳኔ ተደስቶአል። ይህን የኦሮሞን ሕዝብ ውሳኔ ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ ራሱ ለመቀልበስ ካልወሰነ በስተቀር ከተፈጥሮ ኃይል ሌላ ምድራዊ ኃይል ሊያገባው አይችልም። ስለዚህ ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነትም ሆነ ለሕዝቦቿ በጋራ ለመኖር የሚበጀው የብሄር ብሄረሰቦችን የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት ያለምንም ገደብ አውቆ ሰላምና እኩልነት በሰፈነበት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ በጋራ ለመኖር ራስን ማዘጋጀት ትልቅ ጸጋ ነው ባይ ነኝ።

የኦሮሞ ሕዝብ የላቲንን ፊደል ተውሶ ጠቀሜታ ላይ ካዋለ ይሄው ሩብ ምዕት ዓመት አለፈ። በታሪክ የጊዜ መለኪያ ከተለካ በዚህ ረጅም በማይባልበት የጊዜ ገደብ ውስጥ የኦሮምኛ ቋንቋ ሥነ ጽሁፍ ጎልምሶ አድጎ በዓለም ዙርያ አሉ ከሚባሉት ቋንቋዎች እኩል ተሰልፎ መቶ በመቶ የህዝቡን ፍላጎት እያረካ ይገኛል። የኢትዮጵያ ፕረዚዴንት እንኳ ሳይቀሩ ከግእዝ ፊደል በተጨማሪ የባእድ የላቲን ፊደል መጠቀሟ ትክክል ያልሆነ መታረም የሚገባው ጉዳይ መሆኑን በአደባባይ ቢወቅሱና፣ ቢገስጹም  ዕድሜ ለአርቆ አሳቢው ትውልድ እንጂ፡ ዓለማዊ ሥነ ጽሁፎች ብቻ ሳይሆን ዉዳሴ ማርያም፡ ድርሳነ ሚካኤል፡ ገድለ ጊዮርጊስ እና ሌሎችም የቅዳሴ መጻህፍት እንኳ ሳይቀሩ በላቲን ፊደል ታትመው የተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ኦሮሞ ምዕመናንን መንፈሳዊ ጥም ለመጀመርያ ጊዜ አርክቶላቸዋል። የኦሮሞዎች የላቲን ፊደል መዋስ ድሮም ቢሆን ያላሳሰባቸው ባገሪቱ የሚገኙት የተለያየ ብሄረ ሰብ ቋንቋ የሚናገሩ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የየራሳቸውን ቋንቋ እየተናገሩ ግን ደግሞ ባንድነት ሆነው የወያኔን መንግሥት አፍርሰው በምትኩ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት እጅ ለእጅ ተያይዘው ጉዞ ከጀመሩ ሰንብተዋል። የነፕሮፈሰር ውትወታም አላዘናጋቸውም። ግመሎች እያለፉ ነው፡ ምኖቹም ይጮሃሉ ነው ያለው አቶ መለስ – ነፍሱን አ(ይማረውና)! ስለዚህ በኔ ግምት የዛሬው አንገብጋቢ ጥያቄ የኦሮሞዎች የላቲንን ፊደል መዋስ ሳይሆን የወያኔ ሕዝቦቻችንን በታሪካችን ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ እያሰረ እያሰቃየ እየገደለ ያለው መሆን አለበት።

ውድ ፕሮፈሰር – ስለ ኢትዮጵያ አንድነት እንደው ዝም ብለው ያለአንዳች ምክንያት አይባንኑ። ኦሮሞዎች የላቲንን ፊደል በመዋሳቸው አባቶቻቸውና ቅድመ አያቶቻቸው በደምና አጥንታቸው የገነቧትን ኢትዮጵያን ለማንም ጥለው  የትም አይሄዱም። ያለ ኦሮሞዎችና ኦሮምያ ደግሞ ኢትዮጵያ የምትባል አገርም መኖሯ ስለሚያጠራጥር በዚህ አፍራሽ ሃሳብ ዙርያ በመወያየት ጊዜ ከመፍጀት ይልቅ ባንገብጋቢዎቹና የጋራ በሆኑ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ብንረባረብ የተሻለ ይመስለኛል። የላቲን ፊደል እንደሆነ ከኦሮምኛ ቋንቋ ጋር እጅና ጓንቲ ሆኖ ተጠቃሚው ሕዝብም የቋንቋውን ማደግ እያየ በመደሰት ላይ ነውና እርስዎም ዳር ቆመው በማይቸግር ነገር ከሚቸገሩ ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ተቀላቅለው ደስታውን ቢጋሩት ይሻልዎታል ባይ ነኝ።

  1. ያለፈውን ሃያ አምስት ዓመት ጉዞ አዎንታዊ ጎኑን ካየን ደግሞ ኦሮምያ በግልፅ በኢትዮጵያ ካርታ ላይ ተተክላለች፡ ኦሮምኛም በላቲን ፊደል እየተጻፈ የተጠቃሚውን ሕዝብ የረጅም ዘመን ጥማት እያረካ ይገኛል። እነዚህን ሁለት ዕውኔታዎች ካሁን በኋላ ማንም ሊቀለብሳቸው አይችልም። እኛ ኦሮሞዎችም ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን አዲሲቷን ዲሞክራቲክ ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስፈልገውን ሲሚንቶና አሸዋ ጣሪያና ብሎከት እያሰባሰብን መሰረቱን ለመጣል ደፋ ቀና እያልን ነው። የወያኔ መንግሥት መሰናክል ባይሆንብን ኖሮ ባሁኑ ሰዓት ቤቱን ጨርሰን ማስረክብ ነበብን። ግን ተስፋ አንቆርጥም። “ይዘገያል እንጂ እንበሳዋለን” አለች አሉ ጥንዚዛ! ወያኔም እንደማንኛውም መንግስት መጀመርያና መጨረሻ አለው። ስለዚህ ዉድ ፕሮፈሰር – ውድ ጊዜዎንና ብሩህ ጭንቅላትዎን በአስፈላጊ ቦታና አስፈላጊ ጊዜ ለአስፈላጊ ጉዳይ ይጠቀሙ። በቸር ይግጠመን።

 የዚህን ጽሁፍ ደራሲ በ wakwoya2016@gmail.com ማግኘት ይቻላል።

 ጄነቫ, 30 April, 2017

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here